የዚህ ዘመን ነህምያ

መግቢያ
በዚህ ባለንበት ዘመን በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ በግልጽ የሚታየው ችግር ወይም የፈረሰው ቅጥራችን የሀገራችን በሮችና አጥሮች ሳይሆኑ የኢትዮጵያውያን ማንነታችን እና መገለጫችን የሆነው መንፈሳዊ ማንነታችን ነው፡፡ 
በምእራባውያን ፍልስፍና እና ማንነት የተጠመደ እና የተደባለቀ ህይወት ይዘን የእግዚአብሔር ምድር የሆነችውን ሀገራችንን እያረከስናት ነው በዚህ ምክንያትም ቅጥራችንን አፍርሰናል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር እንደ ሰራ ሁሉ አዳም በበደለ ጊዜ ሰው ከማንነቱ ከኤደን ገነት እንደተባረረ እንደተለየ ሁሉ ዛሬም እኛ ኢትዮጵያውያን ከእግዚአብሔር ሀሳብና ፈቃድ ለቀቅ ስንል የገነባውን ቅጥር እናፈርሰዋለን ለጠላትም ክፍት እናደርገዋለን፡፡ 
ነህምያ የፈረሰውን የኢየሩሳሌም ቅጥር በድንጋይና በአፈር በእንጨትም በሩን እንደሰራ የፈረሰውንም በእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳስተካከለ ሁሉ እኛም ኢትዮጵያውያን ከነህምያ ትምህርት በመውሰድ የፈረሰውን ቅጥራችን ማለትም መንፈሳዊ ህይወታችንን የጸሎት ህይወታችን የሃገር ፍቅራችንን የህብረትና የአንድነት ስሜታችንን አጠንክረን ልንገነባ ይገባናል፡፡

መጽሀፈ ነህምያ
ነህምያ የወገኖቹ ለቅሶ የሚያስለቅሰው ህመማቸው የሚያመው ስለራሱ ብቻ ሳይሆን ስለሌሎቹም ወንድምና እህቶቹ የሚኖር ሰው ሰው ነበር፡፡ የነህምያን የፍቅር በመጀመርያዎቹ የመጽሃፉ ምእራፎች ላይ የምንረዳ ሲሆን ነህምያ በሱሳ ግንብ ተቀምጦ ሳለ አናኒ እና ሌሎች ሰዎች መጥተው የኢየሩሳሌም ቅጥር እንደፈረሰ አይሁዶችም በታላቅ መከራ ውስጥ እንዳሉ ሲነግሩት ለረጅም ጊዜ አዝኖ ተክዞ በለቅሶ በጾምና በጸሎት ሁሌ ወደ አምላካችን እጆቹን ይዘረጋ ነበር፡፡ 
ከነህምያ ህይወት እኛ የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን ልንማረው የሚገባን ሌላው ትልቁ ነገር የጸሎት ህይወትን ነው ˝ የአባቶቼ መቃብር ያለባት ከተማ ተፈትታለችና በሮችዋም በእሳት ተቃጥላለችና ፊቴ ስለምን አይዘን˝ ብሎንጉሱ ለምን አዘንክ ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ ከመለሰ በኃላ ምን እንደሚፈልግ ሲጠይቀው ነህምያ ያስቀደመው ወደ አምላኩ እጆቹን ለጸሎት መዘርጋት ነበር፡፡ አዎ ይህ የኛ ትውልድም እንደ አባቶቻችን እንዲሁም ከነህምያ እንደተማርነው ሁሌም በሕይወታችን ውስጥ ስለሃገራችን እጆቻችንን ለጸሎት ከፍ ማድረግ ይገባናል፡፡

የአባቶቻችንን የደበዘዘ ስልጣኔ እና ምስጥራዊ ጥበባት ዳግም በመለስ ሃገራችን ከገባችበት ማቅ ውስጥ ለማውጣት በምናደርገው ጉዞ ሁሉ ሃያላን መንግስታትም ሆኑ ሃገር በቀል ጸረ ኢትዮጵያውያን ቅርጽ ሊያሲዙን ይሞክሩ ይሆናል አልያም በሆነውም ባልሆነውም ቅሬታ በማቅረብ ሊያሰናክሉን ስለሞከሩ ብቻ ከመንገዳችን ልንሰናከል አይገባንም ለዚህም ደግሞ ነህምያ ጥልቅ ትምህርት ይሆነናል ምክንያም እርሱ ሀገሩን ለማቅናት በሚሞክርበት ጊዜ ሐሮናዊው ሰንባላጥ ባርያውም አሞናዊው ጦቢያ ዓረባዊውም ጌሳም በንቀት በተሳለቁበት ወቅት እርሱ ግን ኢየሩሳሌምን ለማቅናት መጥቷልና ፊቱን ወደ አላማው ብቻ ነበር ያዞረው፡፡ እርሱ በህይወቱ ቦታ የሚሰጠው እንዲሁም ማንኛውንም አይነት መልስ የሚቀበለው ከእግዚአብሔር ብቻ ነበር(ነህ 2፡20) እኛም ከዚህ ልንማር የሚገባን ሰዎች ከሚሰጡን መልስ ይልቅ የእግዚአብሔርን መልስ ማስቀደምን ነው፡፡

በነህምያ መጽሀፍ ምእራፍ 3 ላይ የቅጥሩ ሰራተኞች ሊሰሩ እንደተነሱ እና ስራቸውንም ተከፋፍለው ቅጥሩን እንደአደሱና እንደገነቡ በስፋት የተዳሰሰ ሲሆን በሀምሳ ሁለት ቀናት ውስጥ ቅጥሩን ገንብተው ጨርሰዋል፡፡
የዚህ ዘመን ነህምያ ማን ነው ?
የዚህ ዘመን ነህምያ እኛ እራሳችን ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ ነህምያ የፈረሰውን የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደገነባ እኛም የዛሬ ነህምያዎች የፈረሰውን ቅጥራችንን ልንሰራና ልንገነባ ይገባናል፡፡ 

ይህ ማለትም ፡ ከራስ ጥቅም ይልቅ የሃገር ጥቅምን ማስቀደም
፡ የዘረኝነት እና የጎጠኝነት ፖለቲካ አስሽቀንጥረን በመጣል የህብረትና የአንድነት ስሜታችንን ማጠናከር
፡ የምእራባውያንን የኖሩ ዘይቤና ፍልስፍናን ወደጎን በማድረግ ኢትዮጵያዊ የሆነ የኑሮ ዘይቤያችንን
እና ፍልስፍናዎች አጥብቆ መያዝ
፡ እንደ አባቶቻችን እግዚአብሔርን በመፍራት ህይወት ውስጥ መመላለስ ናቸው፡፡

ከነህምያ የተማርነው ቁምነገር ለውጤታማ ስራ ያበቃው ቀዳሚው ነገር እግዚአብሔርን እያሰበ መኖሩ ነው ኢየሩሳሌምን አለመርሳቱ ነው ምክንያም ስራ በተግባር ከመገለጡ በፊት በህሊና ሊታሰብ በልቦና ሊያድር ይገባዋል፡፡ የነጮች አብረቅራቂ ነገር አልያም የተለያየ የኑሮ ሁኔታችን እግዚአብሔርን እና ቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያን ሊያስረሱን አይገባንም፡፡ ለዚህም ነው ˝ . . .በበላህና በጠገብክ ጊዜ በዚያን ጊዜ ከግብጽ ምድር ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ የሚል ተጠንቀቅ. . . ˝ የሚል ኃይለ ቃል ለቤተ እስራኤላውያን የተሰጣቸው( ዘዳ 6፡11-2)፡፡
ሌላው ከነህምያ የምንማረው ስለአባቶቹ አገር ስለኢየሩሳሌም ሲነግሩት ልቡ በሃዘን የተነካው ዓይኑ የእንባ ምንጭ የሆነለት ኅሊናዊ ዝግጅቱ የሁልጊዜ ስለነበር ነው፡፡ በልቦናው ዘወትር እግዚአብሔርን የሚያስብ ሰው በመሆኑ ጥቂት ሲሰማ ብዙ አድርጎ ለመስራት ተሰናዳ ለህዝቡ ሁሉ እስኪገለጥ ድረስ የልቡ ሃዘን በፊቱ ላይ ተነበበ ታዲያ እኛም ኢትዮጵያውያን የሃገራችን የቀደም ማንነትና ሃያልነት ዳግም ለመመለስ በምናደርገው ጥረት ሁሉ ህሊናዊ ዝግጅት ያስፈልገናል እግዚአብሔርን ዘወትር እያሰብን በቢጸ ሀሳውያን እና በአረማውያን እየተወረወረብን ያለውን ቀስት አባኖን ሃገራችንን እና በምድራችን ውስጥ የሚገኙትን ምስጢራትና ሃብታት ጋሻ ሆነን ልንጠብቃቸው ይገባል፡፡

ሁላችንም ˝ አንድ ሰው ራሱን ከመውቀስ የበለጠ ሌላ በጎ ምግባር የለውም˝ የሚለውን የአባቶቻችንን ምክር ተቀብለን ˝ አንተ ማን እንደሆንክ አሳውቀኝ የእኔን ማንነት ግለጥና˝ እያሉ ዘወትር እንደሚጸልዩት አባቶች የእግዚብሔርን ፍጹም ቸርነት ዳግመኛም የራስን ፍጹም ድካምና ውደቀትየምናስብበት ትሁት ልቦናን አንግበን የፈረሰውን ቅጥራችን ገንበትን የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን ለማድረግ መንገዳችንን መጀመር አለብን፡፡ እግዚአብሔር ልንሰራ እንደመረጠን ተናግሯል ስለዚህ ማንንም ሳንጠብቅ ለተጠራንበት ስራ ዛሬውኑ ለስራ መነሳት አለብን ሁላችንም በምንችለው የሚጠብቅብን የዜግነት ሃላፊነታችን ልንወጣ ይገባናል፡፡
ሃገራችን ኢትዮጵያ ለጠላቶቿ ተጋልጣ ነው ያለችው ስለዚህ በእግዚአብሐየር ተመክተን እንደርሱ ፈቃድ በሚገባን ጊዜ የሚገባንን ልናደርግ ይገባል ይህ ማለት ግን ለሁሉም ጊዜ አለው የሚለውን የጠቢቡን ቃል መዘንጋት የለብንም(መክ 3)፡፡ በህብረት መስራት አንድነትና ፍቅርን ይጨምራል፡፡ ፍቅር ደግሞ የሁሉም ነገር መሰረት ነው ክርስቶስ ስለ እኛ ሲል ወደ ምድር የመጣው ፍቅር አስገድዶት ነው፡፡ ፍቅር የማያስችሉ ነገሮችን የማስቻል ስልጣን እና ሀይል አለው ስለዚህ የጥንቷን ኢትዮጵያ ዳግም ለመመለስ በምናደርገው ጉዞ ከእግዚአብሔር ልጆች ከእህት ከወንድሞቻችን ጋር በአንድነትና በፍቅር ልንሰራ ይገባናል(1ቆሮ 13)፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

Leave a comment